በክልሉ ገቢን የመሰብሰብ አቅምን በማሳደግ እና ህገወጥነትንና ሙስናን በመዋጋት የህዝብን ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ
የክልሉ ካቢኔ በመጀመሪያ ሩብ አመት እቅድ አፈፃፀም እየገመገመ ሲሆን በግምገማው ሁለተኛው ቀንም በተለያዩ ተቋማት በሶስት ወራት ውስጥ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት በሚመለከት ሪፖርት ቀርቦ በመድረኩ ተገምግሟል።
ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ኦርዲን በድሪ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመዋጋት ስራዎችን በእቅድ በመምራትና ውጤትን መሰረት ያደረጉ ተግባራት ማከናወን ያስፈልጋል።
የክትትል እና ድጋፍ ማጠናከር፤ የመንግስት የስራ ሰዓት እንዲከበር ማድረግ እንዲሁም አቅምን የማጎልበት ስራዎች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው መልካም አፈፃፀም ላስመዘገቡና አርዓያ የሆኑ ፈፃሚዎችን ማበረታታት ይገባል ብለዋል።
ገቢን በአግባቡ መሰብሰብ የህልውና ጉዳይ ስለመሆኑ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ በእያንዳንድ የገቢ ማሰባሰብ ተግባር ላይም የህግ የበላይነትን በማስከበርና ፍትሀዊ የሆነ የግብር አሰባሰብ ስራ ማከናወን ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ህገወጥነትን በመከላከል ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ እየተደረገ የሚገኘው የቁጥጥርና ክትትል ስራ ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
በግብርናው ዘርፍም የአረንጓዴ አሻራ፣ የሌማት ትሩፋት እና የእንስሳት ተዋፅዖ የማሳደግ ስራዎችም በላቀ ትኩረት እንዲከናወኑ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የግል የትምህርት ተቋማት የሚሰጠው ትምህርትና ስልጠናዎችን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ጥራት ባለው መልኩ እየተሰጡ ስለመሆኑ መመዘን እንዲሁም ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው ያመላከቱት።
የክልሉ ህዝብ ቀልጣፋና ውጤታማ የሆነ አገልግሎት ተደራሽ ማድረግና የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።
Sources HGCA