የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በእለቱም በክልሉ እየተከናወነ የሚገኘው የመብራት ማስፋፍያ ፕሮጀክት ያለበት ደረጃ፤ የጁገል አለም አቀፍ ቅርስ ዙሪያ አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት እና ህገወጥ ግንባታና የመሬት ወረራን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እንዲሁም ሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ተጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅትም ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት በክልሉ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያጎለብቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በክልሉ ትኩረት ከተሰጣቸው የመሰረተ ልማት ስራዎች መካከል አንዱ የመብራት ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው ይህም በተለይ የሀረር የአለም ቅርስነቷን በጠበቀና የህብረተሰቡን የመብራት ችግር ሊፈታ የሚችል መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ከህገወጥ የቤቶች ግንባታ እና የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን በሚመለከትም ህገወጥ የቤት ግንባታና የመሬት ወረራን መከላከል የሁሉም ሀላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በተለይም የደንብ ማስከበር ተቋም ጠንካራ አደረጃጀት ተግባራዊ በማድረግ እና ከፍትህ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ስራ ማጠናከር ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል።
ከጀጎልና ዙሪያው የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ጋር በተያያዘም ከተማዋን ምቹና ፅዱ ከማድረግ አንፃር በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አንስተዋል።
በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች በታቀደላቸው ጊዜና ጥራት እንዲከናወኑ ከማድረግ አንፃር የሚመለከታቸው አካላት በሀላፊነት እና በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ ነው ያመላከቱት።
በጉብኝቱ ላይም የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።