የሀረሪ ክልል ምክር ቤት የ2019 በጀት 12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።
ምክር ቤቱ በሁለተኛው ቀን ጉባኤ ከክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ለ2019 በጀት ዓመት ከ12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አጽድቋል።
የበጀት ረቂቁን ለምክር ቤቱ ያቀረ ቡት የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሃላፊ አቶ መሀመድ ያህያ ናቸው።
ከበጀት ድልድሉ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው የካፒታል በጀት ሲሆን፤ 65 በመቶ ድርሻ ያለው እንደሆነ ተገልጿል።
እንዲሁም 35 በመቶው ለመደበኛ ወጪ ተመድቧል።
በጀቱ የክልሉን የልማት ፍላጎት ለማሳደግ ታሳቢ ተደርጎ የተመደበ ሲሆን፣ በተለይም በ2018 የበጀት አመት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ እንዲሁም በገጠርና በከተማ የሕዝብን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ሊመልሱ በሚችሉ ተግባራት ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ለገጠር እና ለከተማ ኮሪደር ልማት፣ ለንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ለትምህርትና ጤና ሁሉን አቀፍ የልማት ሥራዎች በተሳለጠ መንገድ ለማቅረብ የሚያስችል በጀት መሆኑም ተገልጿል።
የምክር ቤቱ አባላትም በጀቱ በአብላጫው የተያዘው ለካፒታል ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው ይህም የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ በጀት አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።









